Sunday, December 23, 2012

ምርጫ ቦርድ ለመድረክ ግንባርነት ዕውቅና ሰጠ


በዮሐንስ አንበርብር

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መድረክ በሚል ስያሜ ሲንቀሳቀስ ለነበረው የስድስት የተለያዩ ፓርቲዎች ስብስብ ላቀረበው የግንባር አደረጃጀት ጥያቄን በመቀበል ሕጋዊ ዕውቅና ሰጠ፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሐምሌ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ መድረክ ከፓርቲዎች ስብስብነት ወደ ግንባር አደረጃጀት ለመሸጋገር መወሰኑ ይታወሳል፡፡

በዚህም መሠረት መድረክ ለግንባር ምሥረታ የሚያበቁት ዝግጅቶች አጠናቆ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረባቸው ሰነዶች በፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 573/2000 መሠረት የተሟሉ በመሆናቸው፣ ቦርዱ ከታኅሣሥ 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ግንባርነት መሸጋገሩን በመጥቀስ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ የሺ ፈቃደ ቦርዱ የግንባርነት ዕውቅና መድረክ ላቀረበው ጥያቄ መስጠቱን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የፀደቀ መሆኑን፣ የፖለቲካ አጀንዳውንና የገንዘብ አቅሙን በመገምገም ብቁ ሆኖ በመገኘት መድረክ ያቀረበው ጥያቄ በቦርዱ ተቀባይነት ማግኘቱን ወ/ሮ የሺ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል በመድረክ ሥር የነበሩ ፓርቲዎች ስምንት ሲሆኑ ሁለቱ ባለመስማማት በመውጣታቸው ወደ ግንባር ለመሸጋገር የወሰኑት ስድስት ፓርቲዎች ናቸው፡፡

በመሆኑም የግንባሩ አባል የሚሆኑት ፓርቲዎች ዓረና፣ ኦፌዴን፣ ኦሕኮ፣ አንድነት፣ ኢሶዴፓና የደቡብ ኅብረት ናቸው፡፡

የመድረክ የፓርቲ ፕሮግራም አለመቀየሩን የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ለሪፖርተር ገልጸው፣ ጋራ በግንባር ለመሥራትና ባልተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ወደፊት ለመነጋገር በመወሰኑ የዕውቅና ጥያቄው ለምርጫ ቦርድ ሊቀርብ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 እና መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ይሆናል በሚሉት ጉዳዮች አባል ፓርቲዎቹ የማይግባቡባቸው ቢሆኑም፣ እነዚህ ልዩነቶች ቢኖሩም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስፈን ነፃና ሰላማዊ ምርጫ በሚፈጠርበት ሁኔታ ላይ ያለ ልዩነት ለመሥራት ስምምነት መድረሱን ዶ/ር ነጋሶ ገልጸዋል፡፡

ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከተፈጠረ የተለያዩባቸው ነጥቦች ሕዝብ የሚያነሳቸው ጉዳዮች በመሆናቸው፣ ወደ ሕዝብ በማውረድ ወደፊት መነጋገር ይቻላል ብለዋል፡፡ ስምምነት ከተደረሰም ግንባሩ ተዋህዶ አንድ ፓርቲ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment