በአዲስ አበባ ምርጫ ለመሳተፍ አልወሰነም
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ የተደረገው የኃላፊነት ምደባ ሽግሽግ እንጂ የሥልጣን ሽግግርም ሆነ የመተካካት ይዘትና ቅርፅ የለውም አለ፡፡
ኢሕአዴግ ቀደም ሲል ሲፈጽማቸው የቆየው ሕገወጥና የአፈና ተግባራት በአዲሱ አመራርም ተባብሰው ቀጥለዋል ሲል አስታውቋል፡፡
መድረክ ባለፈው ዓርብ አመሻሽ ላይ በዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በመንግሥት ሚዲያ እየተነገረ ስላለው የሥልጣን ሽግግርና በአገሪቱ ውስጥ ተስፋፍተዋል ስላላቸው ወቅታዊ ችግሮች አንስቶ ገዥውን ፓርቲ ተችቷል፡፡
‹‹በኢሕአዴግ ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ምደባ ሽግሽግ እንጂ የሥልጣን ሽግግር አልተካሄደም›› በሚል መሪ ቃል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መድረክ እንዳለው፣ የአቶ መለስን ሕልፈት ተከትሎ የመጣው አዲሱ አመራር በቅርፅም ሆነ በይዘት ሲመዘን ምንም ዓይነት የሥልጣን ሽግግርና የመተካካት መልክ የለውም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ መድረክ አደረግኩት ባለው ግምገማ፣ ‹‹በክቡር አቶ መለስ ሞት ምክንያት በኢሕአዴግ አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ከግለሰቦች ሽግሽግ አልፎ የሚኖር ለውጥ እንደማይኖር ነበር፤›› ያለው ዕውን መሆኑን አስታውቋል፡፡ ‹የታላቁ መሪያችንን ፈለግ ሳናዛንፍ እንቀጥላለን፤›› በሚል ቃል እየገቡ ነው ያላቸው ካድሬዎችና አዲሰ ተሿሚዎችም ‹‹እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ›› ፉክክር ውስጥ መግባታቸው አሳሳቢ መሆኑን አስምሮበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሥልጣን ዘመናቸው ‹‹አፋቸውን አስያዟቸው›› ለመባል በፓርላማ ንግግራቸው ‹‹እጅ እንቆርጣለን›› የመሳሰሉ ማስፈራሪያ አዘል ንግግሮች ሲያደርጉ መኖራቸውን ያወሳው መድረክ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር በመድረክ ላይ ‹‹እሳት መርገጥ ነው›› የሚል ንግግር ማድረጋቸው፣ ‹‹እውነትም የታላቁ መሪያቸውን ፈለግ ሳያዛንፉ መከተላቸውን ያሳያል፤›› ብሏል፡፡
መድረክ በመግለጫው ትኩረት የሰጠው ሌላ ጉዳይ የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን በተመለከተ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ግንባሩ አዋጁን ለመፈረም ፈቃደኛ ባለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ሳይሆን መቀጠሉን ነው፡፡ አሁንም በቅርቡ በናዝሬት (አዳማ) በተደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር ጉባዔ ላይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተስማምተውታል ተብሎ በመንግሥት ሚዲያ የቀረበውን የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ፣ የመድረክ የአመራር አባል ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ግልጽ የሆነ ማደናገሪያና ቅጥፈት ብለውታል፡፡ በዚሁ የማደናገሪያ ስልት መሠረት ኢሕአዴግ ቀደም ሲል በፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈረም ያቀረበው ሰነድ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎችን ቆርጦ መሆኑን ገልጸው፣ በምርጫ 2002 ምርጫውን ለማጭበርበር የተጠቀመበት መሣርያ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ “የዚሁ የቅጥፈት ስልት ሰለባ አንሆንም፤” በማለት፡፡
አሁንም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በማስገንዘብ መድረክ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ሲያቀርበው የቆየው ጥያቄ ችላ መባሉንም በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡ ኢሕአዴግ ቀድሞውንም ይታወቅባቸዋል ያላቸውን ከአሥራ አንድ በላይ ያለ አግባብ በሥልጣን መገልገል ተግባራት ዘርዝሮ በመግለጫው ላይ አስፍሯል፡፡
በሕጋዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ላይ የሚያካሄደው አፈናና ሥርዓት አልበኝነት ተጠናክሮ መቀጠሉን፣ በመላ አገሪቱ ‹‹አንድ ለአምስት›› በሚል አደረጃጀት አንዱ ሌላውን እንዲሰልለው እየተደረገ መሆኑን፣ ሥራ ፈላጊ ምሩቅ ወጣቶች በመንግሥት ተቀጥረው እንዲሠሩ በሊግ ወይም በፌዴሬሽን መደራጀታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ እንዲያቀርቡ መመርያ መተላለፉን መድረክ ከጠቀሳቸው ከቀዳሚዎቹ መካከል ናቸው፡፡
በፕሬስ ነፃነት ላይ እየተወሰዱ ያሉ ሕገወጥ ያላቸውን ተግባራት፣ በሐሰት ክስ በሽብርተኝነት ስለተከሰሱ የፖለቲካ እስረኞች፣ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መደረጉንና ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች አግባብ ያለው መፍትሔ አለመሰጠቱም ከዝርዝሮቹ መካከል ናቸው፡፡ ‹‹ሕገወጥ ግንባታ›› በሚል ሰበብ በውድቅት ሌሊት ቤት የማፍረስ የጭካኔ ዕርምጃ ተፈጽሞባቸዋል ያላቸውን የአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎችን የጠቀሰ ሲሆን፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬት በነፃ ሊባል በሚችል ክፍያ ለውጭ ባለሀብቶች እየተሰጠ መሆኑን በመግለጫው ላይ አስፍሯል፡፡
በአጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱን ጨምሮ በኅብረተሰቡ ውስጥ አሉ ያላቸውን ዘርፉ ብዙ ችግሮች ከገዥው ፓርቲ ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ›› እና ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› ቀኖናዎች የመነጩ ናቸው ብሏቸዋል፡፡ የመድረክ አመራሮች፣ ‹‹እነዚህ ችግሮች የሚያሳዩት በኢሕአዴግ ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የሥልጣን መደላደል እንጂ ሽግግር ወይም ለውጥ እንደሌለ ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ ‹‹አባሎቼና ደጋፊዎቼ›› የሚላቸውን ሹመኞች ለመጥቀም የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሊሳካላት እንደማይችል እርግጠኛ መሆን ይኖርበታል ሲል መድረክ በመግለጫው ገልጿል፡፡ መድረክ መላው ሕዝብ ለሰብዓዊ መብቱና ነፃነቱ መከበር ከእሱ ጋር እንዲሰለፍ የጠየቀ ሲሆን፣ ‹‹ትግሉን ከመቼውም ጊዜ በላይ በማፋፋም እንዲንቀሳቀስ›› ሲል ሕዝባዊ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የመድረክ አመራሮች ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም በተለይ በመጪው የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫዎች መድረክ ይሳተፍ እንደሆነ ተጠይቀው፣ ‹‹አሁን መወሰን አንችልም›› ብለዋል፡፡ ‹‹በተጠቀሱት አገራዊ ችግሮች ላይ በቅድሚያ መነጋገር እንፈልጋለን፤›› ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አሁን ስለ ምርጫው ተሳትፎ መልስ መስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡
የመድረክ አባል በሆኑት ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ አለመቻላቸውንና አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ምስል መፍጠር አለመቻላቸውን አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን አቻችሎ የሚሄድና በተስማማባቸው ጉዳዮች ላይ አብሮ መሥራት የሚችል ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መሬት መሸጥ መለወጥንና አንቀጽ 39 የመሳሰሉት እልባት ያላገኙ ልዩነቶች መድረክ ሥልጣን ከያዘ ለሕዝበ ውሳኔ ለማቅረብ ዕቅድ እንዳለው አክለው ገልጸዋል፡፡
www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment